• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

ደጃች ውቤ ሠፈር ሊፈርስ ነው

September 25, 2013 10:05 pm by Editor Leave a Comment

“በቅርስነት ሊጠበቅ ሲገባው በድንገት ሊፈርስ ነው መባላችን አሳዝኖናል” የአካባቢው ነዋሪዎች

ከአዲስ አበባ ከተማ ምሥረታ ጋር ተያይዞ በቀደምትነት ከተመሠረቱ አካባቢዎች ቀዳሚነቱ የሚነገርለትና በተለምዶ “ውቤ በረሃ” በሚል መጠሪያ የሚታወቀው ደጃች ውቤ ሠፈር፣ በከፊል የሚፈርስ መሆኑ ለነዋሪዎች ተነገራቸው፡፡

በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ አምስት ንዑስ ቀበሌ 05 ከጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት ወደ አፍንጮ በር በሚወስደው መንገድ በቀኝ በኩል በ11.6 ሔክታር ቦታ ላይ ያሉ ነዋሪዎች እንደሚነሱና ከ100 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው ሠፈር እንደሚፈርስ ለነዋሪዎቹ የተነገራቸው፣ መስከረም 11 ቀን 2006 ዓ.ም. በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ለግማሽ ቀን በተደረገ ውይይት ነው፡፡

ከራስ መኮንን ድልድይ ወደ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በስተቀኝ በኩል በሚያስወጣው አስፓልት እስከ አደባባዩ ድረስ የተገነቡ የመኖሪያ ቤቶች፣ የንግድ ቤቶችና የተለያዩ ቢሮዎች፣ ሆቴሎችና ምግብ ቤቶችን ጨምሮ እስከ አፍንጮ በር ድልድይ መዳረሻ ድረስ እንዲፈርሱ ምክንያት የሆነው፣ የባቡር ተርሚናልና ኃይል መስጫ ጣቢያ ሊገነባበት በመሆኑ እንደሆነ በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት በተደረገው የግማሽ ቀን ስብሰባ እንደተነገራቸው ነዋሪዎቹ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ነዋሪዎቹ እንደገለጹት፣ በጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አደባባይ ፊት ለፊት ከሚገኙት ንግድ ቤቶች ጀምሮ ከሦስት ሔክታር በማይበልጥ ቦታ ላይ ያሉ ነዋሪዎች እንደሚነሱ ቀድመው ተነግሯቸዋል፡፡ መስከረም 11 ቀን አስቸኳይና ድንገተኛ ስብሰባ እንዳለና ማንም ቢቀር ኃላፊነቱ የራሱ እንደሆነ በማስጠንቀቅ ነዋሪዎች እንዲገኙ ከተደረገ በኋላ፣ በሰሙት ጉዳይ እጅግ በጣም መደንገጣቸውንና ማዘናቸውን አስረድተዋል፡፡

የባቡር ተርሚናልና ኃይል መስጫ ጣቢያ ግንባታ በሚል በዳር ያሉት እንደሚነሱ በቅድሚያ ከተነገራቸው በኋላ በድንገት “የሚያስፈልገው ስምንት ሔክታር ነው፡፡ የሚቀረው 3.6 ሔክታር ተቆርጦ መቀጠል ስለሌለበት ለመልሶ ማልማት መፍረስ አለበት፡፡ ይኼ ደግሞ ተወስኖ አብቅቷል” መባላቸው ተገቢ አለመሆኑንና ኅብረተሰቡን መናቅ እንደሆነ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡

በቅርስነት ተጠብቆ መኖር ሲገባው እንደ መርዶ ነጋሪ በድንገት እንደሚፈርስ መወሰኑን ለነዋሪዎች ማርዳት ማን አለብኝነት ነው የሚሉት ነዋሪዎቹ፣ ከወረዳ እስከ ማዕከል ድረስ መረጃ በመጠየቅ በሁለትና በአራት ሚሊዮን ብር በቅርቡ ከሚፈርሱት ቤቶች ውስጥ የመኖሪያ ቤትና የንግድ ቤቶችን የገዙትን ለመጉዳት ሆን ተብሎ የተደረገ እንደሚያስመስለውም ጠቁመዋል፡፡

ነዋሪዎቹ እንደተነገራቸው ከሆነ፣ አስተዳደሩ ሁለት አማራጮችን አስቀምጦላቸዋል፡፡ የመጀመሪያው 20 በመቶ ቅድሚያ ክፍያ በመፈጸም የጋራ መኖሪያ ቤት ማግኘት ሲሆን፣ ሁለተኛው አማራጭ የቀበሌ ወይም የኪራይ ቤቶች ተዘጋጅተውላቸው ወደዚያ መግባት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አስተዳደሩ አስቀምጦላችኋል የተባሉትን አማራጭ ነዋሪዎቹ ተቃውመዋል፡፡ ምክንያታቸውም መንግሥት አቅማቸውን በማወቅ 20 በመቶ ቅድሚያ ክፍያ ፈጽመው የኮንዶሚኒየም ቤት ባለቤት ለመሆን አምስት ዓመታትን መጠበቅ ግድ እንደሚላቸው ነግሯቸው፣ ተመዝግበው እየቆጠቡና እየጠበቁ መሆናቸውን ነው፡፡ ይኼ ሆኖ ሳለ በድንገት 20 በመቶ ክፍያ እንዲፈጽሙ መጠየቅ ተገቢ አለመሆኑን አውስተዋል፡፡

ደርግ እንኳን “ሠፈራ” በማለት ነዋሪዎችን ከቀያቸው ሲያስነሳ ባለአንድ ፎቅ ሕንፃ ገንብቶ በማስረከብ እንደነበር የሚናገሩት ነዋሪዎቹ፣ “ምን ያመጣሉ” በማለት ከአራት ወር በኋላ በጥር ወር ውስጥ ለዘመናት የኖሩበት ቤት እንደሚፈርስ ማሳወቅ ተገቢ ባለመሆኑ፣ መንግሥትም ሆነ የሚመለከተው አካል ለነዋሪዎች ክብር በመስጠት ነገሩን እንዲያጤነው ጠይቀዋል፡፡

የነዋሪዎቹን ቅሬታ በመግለጽ ማብራሪያ እንዲሰጡን ያነጋገርናቸው በአራዳ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማት ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ ሙሉጌታ፣ “አስተዳደሩ ወይም መንግሥት ማንንም መጉዳትና መበደል አይፈልጉም፡፡ የደጃች ውቤ ሠፈር ነዋሪዎች ወደ ሌላ አካባቢ እንደሚዛወሩ የነገርናቸው ተማሪዎችን ታሳቢ ባደረገ መንገድ ዕቅዳችንን ነው” ብለዋል፡፡

ነዋሪዎቹ በዋናነት እንዲነሱ የተነገራቸው መንግሥት እያስገነባው ላለው የቀላል ባቡር ፕሮጀክት ከሚያስፈልጉት አራት ተርሚናሎች መካከል አንዱ ፒያሳ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት በቀኝ በኩል እስከ ደጃች ውቤ ሠፈር ስምንት ሔክታር ቦታ ላይ መሆኑን አቶ ግርማ ገልጸዋል፡፡ ጫፍ ላይ ላሉ ነዋሪዎች ቀደም ብሎ የተነገራቸውና ያወቁ ቢሆንም፣ ቀሪዎቹን ማወያየትና ማሳወቅ አስፈላጊ በመሆኑ መስከረም 11 ቀን 2006 ዓ.ም. ማወያየታቸውን የገለጹት ኃላፊው፣ መንግሥት ድርጊቱን እየፈጸመ ያለው ቅርስን ካለመፈለግና ነዋሪዎችን ከማፈናቀል አኳያ መታየት እንደሌለበት አስገንዝበዋል፡፡

ቅርስም ሆነ ሌላ ነገር ከባቡር ተርሚናሉ ጋር የሚገናኝ ከሆነ መፍረሱ የማይቀር መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፣ እንዲፈርስ ውሳኔ የተላፈበት ቦታ 11.6 ሔክታር መሆኑንና ለተርሚናልና ለኃይል መሙያ ስምንት ሔክታር ተወስዶ ቀሪው 3.6 ሔክታር ለመልሶ ማልማት እንደሚውል አቶ ግርማ ገልጸዋል፡፡ ከባቡር ተርሚናል የሚተርፈው 3.6 ሔክታር ቦታ የግል ይዞታ ከሆነና በፕላኑ መሠረት ለመኖሪያ ቤት ወይም ለድርጅት የሚጋብዝ ከሆነ፣ ባለይዞታዎቹ እንዲያለሙት ቅድሚያ እንደሚሰጣቸው አቶ ግርማ ጠቁመዋል፡፡

“ማንም ነዋሪ እንዲንገላታ አንፈልግም፡፡ በፌዴራል አዋጅ ቁጥር 455/97 መሠረት ለልማት ለሚነሱ ነዋሪዎች ሁለት አማራጮችን እናቀርብላቸዋለን” ያሉት አቶ ግርማ፣ አንደኛው በቀበሌ ወይም በኪራይ ቤት የሚኖሩ ከሆነ ከስቱዲዮ እስከ ሁለት መኝታ ቤት የጋራ መኖሪያ ቤት እንዲያገኙና 20 በመቶ ቅድሚያ ክፍያ እንዲፈጽሙ ማድረግ ነው፡፡ ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ በሌላ ቦታ የቀበሌ ወይም የኪራይ ቤት እንዲያገኙ ማድረግ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ነዋሪዎቹ የኮንዶሚኒየሙን ቅድሚያ ክፍያ መንግሥት እንዲከፍልላቸው መጠየቃቸውን የገለጹት ኃላፊው፣ ጥያቄያቸው አግባብነት የሌለውና አሁን የሚኖሩት በትንሽ ክፍያ የነፃ ያህል መሆኑን፣ ቦታውና ቤቱም የመንግሥት በመሆኑ አቅም ከሌላቸው በመመርያው መሠረት በቀበሌ ቤት እንዲኖሩ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡ ወደፊት በጋራ ሕንፃ ላይ መኖራቸው ስለማይቀር ያለዕጣ የማግኘት ዕድላቸውን እንዲጠቀሙ መክረዋል፡፡

የግል ይዞታ ያላቸው ነዋሪዎችን ለመለየትና ለማወቅ ትክክለኛው መረጃ ገና በመሰባሰብ ላይ ቢሆንም ከ105 በላይ እንደሚሆኑ የገለጹት ኃላፊው፣ እነሱም በአዋጅና በመመርያ ቁጥር 3/2002 መሠረት ሁለት አማራጮች እንደተዘጋጁላቸው ተናግረዋል፡፡ አንደኛ አማራጭ በመንግሥት መሬት ላይ የሠሩት ቤት ካሳ ተከፍሏቸው ኮንዶሚኒየም ቤት በቅድሚያ እንዲያገኙ ማድረግ ሲሆን፣ በሁለተኛ ደረጃ ካሳ ተከፍሏቸው በመሀል ከተማ ቦታ እንደሚሰጣቸው ወይም በማስፋፊያ አካባቢ እንዲመርጡ ማድረግ መሆኑን አቶ ግርማ አብራርተዋል፡፡ ነዋሪዎቹ በዚህ ዓመት መጨረሻ ሊነሱ እንደሚችሉ የጠቆሙት ኃላፊው፣ ምናልባት ነገሮች ከተመቻቹ በጥር ወር ሊያሸጋግሯቸው እንደሚችሉ በስብሰባ ላይ እንደነገሯቸው አስረድተዋል፡፡

ከቅርስ አጠባበቅ ጋር በተያያዘ ለተነሳላቸው ጥያቄ አቶ ግርማ በሰጡት ምላሽ፣ “አንዳንዶቹን ከቅርስ አኳያ የምናያቸው አሉ፡፡ በመመርያው መሠረት የሚሆነው ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ያህል ዶሮ ማነቂያ አካባቢ እየተለዩ ነው፡፡ የባቡር ተርሚናሉና ኃይል መሙያው የሚሠራበት ከሆነ ግን ለድርድር አይቀርብም፡፡ ይፈርሳል፡፡ መታሰብ ያለበት ነገር ቢኖር ጊዜያዊውን ችግር ብቻ ሳይሆን ኅብረተሰቡ ወደተሻለ ሕይወት ማለፍ ስለሚኖርበት ነው” ሲሉ አቶ ግርማ ገልጸዋል፡፡

በደጃች ውቤ (ውቤ በረሃ) ሠፈር ከሚፈርሱት ቤቶች መካከል የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ዩኒቨርሲቲ ሲማሩ ይኖሩበት የነበረውና ከራስ መኮንን ድልድይ በስተቀኝ በኩል የሚገኘው ዓድዋ ሆስቴል፣ የታዋቂው አኮርዲዮን ተጨዋች አቶ ፍሬው ኃይሉ ቤት፣ የኢትዮጵያ ባለውለታ የነበሩትና በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን ከቱርክ መሣሪያ በመግዛት ለኢትዮጵያ ያመጡ የነበሩት አርመናዊው ሚስተር ቴራዚያን ቤተሰቦች መኖሪያ ቤት፣ በቀይ ሽብር ቤተሰቦቻቸው የተገደሉባቸው አፈ ንጉሥ ተክሌ ቤት፣ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የነበሩት የጄነራል መልኬ ቤት፣ በደርግ ዘመን የዘመቻ መምርያ ኃላፊ የነበሩት ከበደ ስመኝ ቤት፣ በደርግ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የነበሩት አቶ ቢልልኝ ማንደፍሮ ቤት፣ የመጀመሪያው ስፖርት ቤት መሥራች ሙሉ ስፖርት ቤት፣ የመጀመሪያው የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ በረኛ አቶ ታደሰ ጌጤ ቤት፣ የቡድኑ መሥራችና ተጨዋች የነበሩት አቶ አየለ አትናሸ ቤት ጥቂቶቹ ሲሆኑ፣ በአጠቃላይ ከ775 በላይ ቤቶች እንደሚፈርሱ ታውቋል፡፡ (ሪፖርተር)

Print Friendly, PDF & Email

60

SHARES
Share on Facebook
Tweet
Follow us
Share
Share
Share
Share
Share

Filed Under: Politics Tagged With: Right Column - Primary Sidebar

Reader Interactions

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • ጃዋርና በቀለ መታሠራቸው ተሰማ June 30, 2020 09:17 am
  • አገራዊ መድረክ ውጪ ድብቅ ውይይትን አንቀበልም June 17, 2020 06:57 am
  • ዴክሳሜታሶን! የኮሮና መድሀኒት June 17, 2020 06:49 am
  • የሰኔ 14ቱ ቀለበታዊ የፀሃይ ግርዶሽ በኢትዮጵያ! June 17, 2020 06:38 am
  • የግብፅ የአባይን ውሃ ብቻዬን ልጠቀም ግትር አቋም ድርድር እንቅፋት ሆኗል June 10, 2020 07:15 am
  • የቴድሮስ “ሥልጣን” – የመጨረሻው መጀመሪያ!? April 12, 2020 02:48 am
  • በብዛት የትግራይ ተወላጆች የሚጠቀሙበት የኤርትራ ስደተኛ ካምፕ ሊዘጋ ነው March 18, 2020 08:37 pm
  • እየተፈረካከሰ ያለው አንጋፋው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ March 18, 2020 08:09 pm
  • ኮሮና አዲስ ጉድ መዘዘ – ከቻይና በፊት በአሜሪካ ቁጥራቸው የማይታወቅ ሰዎችን ቀጥፏል March 16, 2020 11:41 pm
  • የኮንዶሚኒየም ቤቶች በደላሎችና በመመሪያ ሰጪዎች ኔትዎርክ እየተቸበቸበ ነው! ታከለ የት ናቸው? March 9, 2020 10:18 am
  • ኤርሚያስ ለገሠ ከባለአደራ ተባረረ March 9, 2020 08:09 am
  • ድፍድፍ ሲቀል ይንሳፈፋል፤ ምሁር ሲዘቅት ይመራል፥ March 7, 2020 11:24 pm
  • ኢትዮጵያዊ ምን ይመስላል? በምንስ ይመሰላል? March 7, 2020 10:29 pm
  • WHY I WROTE “MONEY, BLOOD AND CONSCIENCE” March 4, 2020 11:15 pm
  • አድዋ፤ የጥቁር ሕዝብ ድል! March 2, 2020 11:24 am
  • ፊታውራሪ ገበየሁ ገቦ (አባ ጎራው) March 2, 2020 11:12 am
  • የኦነግ ሁለት መልክና ሦስት ግብሮች – ቃርሚያው ኃይል ቅጥር ነፍሰገዳይ ሆኗል February 25, 2020 11:26 pm
  • በቡራዩ “የጃል ማሮ” ፎቶ ጨረታ አፈናከተ፤ “ቡራዩ ሆኖ ከሃዲን ማሞካሸት አይቻልም” ነዋሪዎች February 17, 2020 09:13 pm
  • “ዲቃላ” የፍረጃ ፖለቲካ በኦሮሚያ የኃይል አሰላለፉን እየቀየረ ነው February 13, 2020 11:58 pm
  • “ከዚህ በኋላ ማናቸውንም በወንጀል ድርጊት ውስጥ የሚሳተፉ አካላትን” አንታገስም – ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ February 13, 2020 05:07 pm
  • “እኛ ማንም ተሳዳቢ እንዲመጣብን አንፈልግም” የጅማ ነዋሪ February 13, 2020 09:28 am
  • “ወላጆቻችሁ ሰላማዊ ሰልፍ በሕዝቡ ያስደርጉልን” – አጋቾች February 11, 2020 07:53 pm
  • “ወንጀል የፈጸመም ያስፈጸመም ተይዞ ለህግ ይቀርባል፤ ምርመራም ተጀምሯል” February 11, 2020 06:59 pm
  • ጃዋር ወደ መጨረሻው “የትግል” ስልቱ – አማራን ማበጣበጥ! February 10, 2020 11:54 pm

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2026 · Goolgule