• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

የጎልጉል ቅምሻ

March 6, 2013 09:29 am by Editor Leave a Comment

“ሐብቴ ቢያንስ 20ቢሊዮን ፓውንድ ነው”

የዓለማችንን ባለጠጋዎች ዝርዝር በማውጣት የሚታወቀው ፎርብስ የተሰኘው መጽሔት የሳውዲ ንጉሥ አብዱላ ወንድም ልጅ የሆኑትን ልዑል አልዋሊድ ቢን ጣላል ያላቸውን ሃብት ዝቅ አድርጎ በመናገሩ ልዑሉ እጅግ ተቆጥተዋል፡፡

የሐብታቸው መጠን ቢያንስ 20ቢሊዮን የእንግሊዝ ፓውንድ እንደሚደርስ የተናገሩት ልዑል በደንብ ከተሰላ መጠኑ 29.6ቢሊዮን ፓውንድ እንደሚደርስ አስታውቀዋል፡፡ ሮልስ ሮይስን፣ ፌራሪን እና ላምበርጊኒስን ጨምሮ ከ200 መኪናዎች በላይ ያሏቸው የ57ዓመቱ ልዑል ጣላል፤ በአውሮጳ እጅግ ውድ የሆኑ ሆቴሎችን ባለቤት ከመሆናቸው አልፎ እጅግ ትልልቅ የሆኑ ሁለት መርከቦች እና የዓለም ትልቁ የግል አውሮፕላን ጀት ባለቤትም ናቸው፡፡ በለንደኑ ሳቮይ ሆቴል፣ በአፕል ኩባንያ፣ በሲቲግሩፕ እና ኒውስ ኮርፕ ያላቸው ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ዋጋው ዝቅ ተደርጎ እንደተገመተ ያስረዱት ልዑል ለሁኔታው ተጠያቂ ነው ያሉትን የመጽሔቱ ዋና አዘጋጅ ከሥራው እንዲባረር ጠይቀዋል፡፡ ጉዳዩንም ፎርብስ ለመካከለኛው ምስራቅ ባለሃብቶች ያለውን የተጣመመ አመለካከት የሚያሳይ ነው በማለት ወንጅለውታል፡፡

በርካታ የዓለማችን ባለጠጋዎች የሃብታቸውን መጠን በይፋ ለመናገር ፈጽሞ የማይፈልጉ መሆናቸው እየታወቀ ባለበት ሁኔታ የልዑሉ ግልጽነት በርካታዎችን አስደምሟል፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት ሃብታቸው በትክክል ቢመዘን ኖሮ ከ26ኛ ደረጃ ወደላይ ከፍ በማለት ከሎሪዬል (የሽቶና ማስዋቢያ አምራች) ወራሽ ሊሊያን ቤተንኩር ቀጥሎ የ10ኛ ደረጃ ይጎናጸፉ ነበር፡፡

ከእስርቤት ወደ ሆቴልቤት

ቦታው ከዚህ በፊት ሰዎች የተቻላቸውን ሁሉ አድርገው ቢቻል መውጣት የሚመኙት ነው፡፡ አንድ ቀን እንኳን ማደር የማይፈልጉበት ነበር፡፡ ከፍተኛ ወንጀል የፈጸሙ እስረኞች የሚታሰሩበትና ላለፉት 150ዓመታት አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው በኔዘርላንድ የሚገኝ እስርቤት ፍጹም ማሻሻያ ተደርጎበት ወደ ሆቴልነት ከተቀየረ ወዲህ ግን ሰዎች በርካታ ቀናት የሚያድሩበትና ቢቻላቸውም ጨምረው መቆየት የሚፈልጉበት ቦታ ሆኗል፡፡

105 የእስረኛ ክፍሎች የነበሩት ወደ 40 ሰፋፊ ያጌጡ የሆቴል ክፍሎች ተቀይረው በክፍሎቻቸው ዘመን አመጣሽ ቲቪዎች፣ ነጻ የኢንተርኔት አገልግሎት፣ … ከውብ መኝታዎቻቸው ጋር አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ ተጠቃሚዎችም ዳጎስ ያለ ገንዘብ በመክፈል ያድሩባቸዋል፡፡

ልማት፣ ሕዳሴ፣ … እያለ ሕዝባችንን የሚያደነቁረው ኢህአዴግ ከልማትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ውስጥ የእስርቤት ግንባታውን ጉዳይ ቢሰርዘው ከሰማን እንነግረዋለን፡፡ በተለይ አሁን ደግሞ ሙስሊሞችን ጥያቄ አቀረባችሁ በማለት በገፍ እስርቤት እያስገባ ከሚያሰቃይና ተጨማሪ እስርቤቶችን ከሚሠራ ጥያቄያቸውን ቢመልስና ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች ለቅቆ የኔዘርላንድን ፈለግ መከተል ከሁሉ የላቀው ህዳሴ ነበር፡፡

“ኪርዛኪስታን” – አዲሷ የጆን ኬሪ አገር

የአሜሪካ ፖለቲከኞች ለሌላው ዓለም ስምና አጠራር እምብዛም አይጨነቁም፡፡ አጣምመው፤ አወላግደው፤ … የአገር፣ የቦታዎችን፣ የመሪዎችን ስም ሲጠሩ ይሰማሉ፡፡

በቅርቡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ጆን ኬሪ ሥልጣን ከመያዛቸው አንድ ወር ባነሰ ጊዜ አዲስ አገር ፈጥረዋል – “ኪርዛኪስታን” የምትባል! በቅርቡ በቨርጂኒያ ዩኒቨርሲቲ ባደረጉት ንግግር የአሜሪካ ወዳጅ የሆነችውን ኪርጊስታንን እና የሰሜን ጎረቤቷ የሆነችው ካዛኪስታንን በመቀላቀል ኪርጊስታንን የጠሩ መስሏቸው ኪርዛኪስታን በማለት ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አዲስ አገር አስተዋውቀዋል፡፡ እንደዚህ አይነት ስህተቶችን በመስራት የሚታወቁት ጆን ኬሪ ከስድስት ዓመት በፊት በኢራቅ የሚገኙትን የአሜሪካ ወታደሮችን ዝቅ የሚያደርግ ቃል ተናግረው አያሌ ሕዝብ ተከፍቶባቸው ነበር፡፡ “ትምህርታችሁን በደንብ ከተከታተላችሁ፤ እንደሚገባው ካጠናችሁ፤ የቤት ስራችሁን ከሰራችሁ ጎበዝ ተማሪ ትሆናላችሁ፤ አለበለዚያ ግን ኢራቅ ተቀርቅራችሁ ነው የምትቀሩት” በማለት ነበር በወቅቱ ለመቀለድ የሞከሩት፡፡ በመጪዎቹ አራት ዓመታት ብዙ ሲሉ እንሰማቸዋለን፡፡

1.6 ሜትር የጾታ ግድግዳ በየሱቁ

ሳውዲአረቢያ በምትከተለው ጥብቅ ሃይማኖታዊ ሕግ ምክንያት የቅርበት ዝምድና የሌላቸው ወንድና ሴት በሙሉ ተለያይተው ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ሰፋፊ ሱቆች 1.6ሜትር (5ጫማ ከ3ኢንች) ከፍታ ያለው ግድግዳ እንዲያቆሙ ታዝዘዋል፡፡ ወንድና ሴት ሠራተኞችን የሚቀጥሩ ሱቆች ይህንን ትዕዛዝ እንዲተገብሩና ሁኔታውንም ሃይማኖታዊ ፖሊሶች (ሙታዋ) እንዲያስፈጽሙ ተነግሯቸዋል፡፡

ሆኖም ጉዳዩ አሉባልታ ነው በማለት ምላሽ የሰጡት የመንግሥት ባለሥልጣን ወንድና ሴት ሠራተኞች የሚቀጥሩ ሱቆች ሁኔታው እንዳመቻቸው የፈለጉትን ማድረግ ይችላሉ በማለት ጉዳዩን አጥላልተውታል፡፡ እስላማዊው ግዛተአጼ በሚከተለው ዋሃባዊ የሻሪያ ሕግ ምክንያት በሳውዲአረቢያ ሴቶች መኪና መንዳት የማይፈቀድላቸው ሲሆን በባንኮችና ቢሮዎች የራሳቸው የመግቢያ በር የሚጠቀሙ እንዲሁም በአለባበስ በኩል ጥብቅ ሥርዓት መከተል ይጠበቅባቸዋል፡፡

በሰሜን አፍሪካ የአረብ ጸደይ የለውጥ ማዕበል ለዘመናት በሥልጣን የቆዩ መሪዎች ከሥልጣን ካስወገደ በኋላ የአሜሪካ ጥብቅ ወዳጅ በሆነችው ሳውዲአረቢያ እጅግ መጠነኛ ለውጦች እየተካሄዱ ይገኛል፡፡ ባለፈው ወር ንጉሥ አብዱላ በምክርቤታቸው አወቃቀር ላይ ማሻሻያ ካደረጉ በኋላ 150 አባላት ከሚገኙበት የሹራ ምክርቤት 30 የሚሆኑት ሴቶች መቀላቀል ችለዋል፡፡

“ሒትለር በአመጋገቡ እጅግ ጠንቃቃ ነበር” ምግብ ቀማሹ

የአዶልፍ ሒትለርን ምግብ ለዓመታ ሲቀምሱ የነበሩ የ95ዓመቷ ጀርመናዊት ሒትለር በአመጋገቡ በኩል እንዴት ጠንቃቃና አትክልትና ፍራፍሬን በታማኝነት ይመገብ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ሒትለር በምግብ መርዝ እንዳይሞት ከፍተኛ ጥበቃ እንዲካሄድ በማስፈለጉ ይህንኑ የምግብ መቅመስ ጉዳይ እንዲያከናውኑ ከተመደቡት 12ሴቶች መካከል አንዷ የነበሩት አዛውንት ሲናገሩ “ከእኩለቀን በፊት ከ5 እስከ 6ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ ሁላችንም ምግቡን እንቀምሳለን፤ ከዚያም ምግቡ ወደኤስ ኤስ ጠቅላይ ጽ/ቤት ይወሰዳል” ብለዋል፡፡ ምግቡ በሙሉ አትክልት እንደነበረና የሥጋ ምግብና አሣ ሲቀርብ እንደማያስታውሱም ገልጸዋል፡፡ ባሳለፏቸው ዓመታት ከባድ ፍርሃት ላይ ወድቀው እንደነበር የተናገሩት ሴት በሆነ አጋጣሚ ምግቡ ተመርዞ ቢሆን ኖሮ እንኳን የመቅመስ ግዴታ ስለነበረባቸው ቀምሰው ሊሞቱ ይችሉ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

የጀርመን ሕዝብ የአትክልት ተመጋቢ እንዲሆን ከፍተኛ ምኞት የነበረው ሒትለር ጦርነቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ዓላማውን ተግባራዊ ለማድረግ ዕቅድ ነድፎ እንደነበር ይነገርለታል፡፡ የአትክልትን ብቻ ምግብነት የሚደግፉ ቡድኖች በተለይ በአሁኑ ጊዜ የሥጋ ውጤቶች በኬሚካልና በሌሎች ሆርሞኖች እየተበላሸ በመምጣቱ የእንስሳትንም ሆነ የዶሮ ሥጋ ለምግብነት መጠቀም ለበርካታ በሽታዎች እንደሚያጋልጥ ይመክራሉ፡፡

“ስለ እናት”

ከዚህ በታች ያለውን ጽሁፍ ያገኘነው ከዮሐንስ ሞላ ፌስቡክ (Yohanes Molla) ነው፡፡ ስለእናቱ የጻፈውን አጭርና እጅግ መሳጭ ጽሁፍ እንዳለ አቅርበነዋል፡፡ ዮሐንስ ለጽሁፉ ርዕስ ባለመስጠቱ “ስለ እናት” ብለን ሳናስፈቅድ ርዕስ በመስጠታችን እንደማይቀየመን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ምስጋናችንም የላቀ ነው፡፡

“… በልጅነቴ ተድሬ ልጅነቴን ሳላውቀው አለፈኝ። ከዚያ በኋላ ግን ከጓደኞቼ ጋር… አሻሮ እየቆላን፣ እንኩሮ እያነኮርን እንጫወት ነበር። ስራችንን ከጨረስን ዝም ብለን እየተቀላለድን እንጫወታለን። እንዘፍናለን። እንጨፍራለን። ልጆች ነን፥ ዝም ብሎ መሳቅ መቀለድ ነው። ግን የግድ ማስተዋልም አለ።… ታዲያ ሁሉም ነገር መሽቶ ባሎቻችን ቤት እስኪመጡ ነው።… ከመሬት ተነስተው ስለሚመቱን እንፈራለን።

ያኔ ሳንቲም እንዳያጥረኝ መሸታ እጠምቅ ነበር። … መጥመቁን ከእናቴ የተማርኩት ነው። እናቴ ትነግዳለች፤ መሸታ ስለምትጠምቅ ብር አይቸግራትም ነበር። እኔም አንድ ልጇ ስለሆንኩ አይከብዳትም መሰለኝ በጣም ትንከባከበኝ ነበር። በልጅነቴ – 9 ዓመት ሲሆነኝ – ሞተች። ታዲያ ግን እርሷ የምትለውን ያምታደርገውን ሁሉንም አስታውሳለሁ። እንደሷ መሆን እፈልግ ነበር።…

ባለቤቴ የቀን ወጪ 30 ሳንቲም ይሰጠኛል። 30 ሳንቲም ብዙ ነው። ቡናውን፣ የቡና ቁርሱን፣ ወጡን፣ እንጀራውን፣ እንጨቱን፣ ሁሉንም በዚያው በ30 ሳንቲም ነው። እርሱን አብቃቅተን እንበላበትና ያልቃል።… ከሆድ አያልፍም ነበር። እንግዳ ቢመጣብኝ እንኳን አንድ ጣሳ ጠላ ገዝቼ ላስተናግድ ብል ስለማልችል ተጨማሪ ፍራንክ እፈልግ ነበር። ለዚያ ነው ጠላ የምጠምቀው። እንደዛ ስለማደርግ ሳንቲም አይቸግረኝም።

የብር ከሃምሳ ጠላ ብጠምቅ፣ ብር ከሃምሳ ትርፍ ያመጣልኝ ነበር። እንግዳ ቢመጣ አላፍርም፤ በደንብ ነው የማስተናግደው። ከጓደኞቼም ጋር አምስት አምስት ሳንቲም እናዋጣና እንጀራ፣ ጠላ ቆሎ ሁሉን ነገር ገዝተን እየበላን እየጠጣን እንጫወታለን። ጨዋታ ሳንጨርስ ስላገባን ዝም ብሎ መጫወት ያምረን ነበር። በየቀኑ ጨዋታ ነው።… እንደዚያም ሆኖ ግን ቤት አለ። የቤት ስራው አለ። ባል ይማታል። ልጅ ማሳደግ አለ።…

በ21 ዓመቴ 3 ልጆች ወልጃለሁ። ራሴ ግን ልጅ ነበርኩኝ። (ትስቃለች) እንኳን ልጅ ላሳድግ ጨዋታም ያምረኝ ነበር። መጀመሪያም ሳልፈልግ ስላገባሁ ሁሌ መፋታት እፈልግ ነበር። አባቴን በመጡ ቁጥር እጨቀጭቃቸው ነበር። ዛሬም አስፈቱኝ። ነገም አስፈቱኝ ነው። እርሳቸውም ‘ልጅነት ነው። ልጅ ስትወልድ ትተወዋለች።’ እያሉ በቀጠሮ ያራዝሙብኛል።

ብልህ ነበሩ፥ ቆይ ለፋሲካ፣ ቆይ ለመስቀል ይሉኛል። እኔም አልረሳም። እውነት መስሎኝ አስታውሼ እጠይቃቸዋለሁ። ለመስቀል ስጠይቃቸው – ‘ቆይ ለፋሲካ’ ይሉኛል። ለፋሲካ ሳስታውስ – ‘ቆይ ለገና’ ይሉኛል። እኔም ሳልረሳ እጠይቃለሁ። ታዲያ ሁለት ልጅ ተከታታይ ሞቶብኝ ሶስተኛውን ልጄ ሳይ የትም መሄድ አስጠላኝ። እንኳን አፋቱኝ ልል ከዚያ ቤት ሞት ይንቀለኝ አልኩኝ። ብማረርም መፋታቱን ማሰብ ተውኩኝ።

ታዲያ ተፋትቼ ቢሆን ኖሮ ይፀፅተኝ ነበር። ይሄን ሁሉ አላይም ነበር። ሳልፈልግ አግብቼ ከእግዚአብሄር ጋር ቤት ሙሉ ልጅ አሳደግሁኝ። … ፀጋው አይጓደል። ምን አጣሁ? ባጣም የማላውቀውን ነው።… ” ~ My Mom ♥


ዘገባውን ለማጠናቀር በየጽሁፉ ከጠቀስናቸው ምንጮች በተጨማሪ ሌሎችንም የሚዲያ ውጤቶች መጠቀማችንን ለመግለፅ እንወዳለን፡፡ ከዜናዎቹ ማነስ አኳያ በየጸሁፉ ለመግለጽ ባለመቻላችን ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡

Print Friendly, PDF & Email

60

SHARES
Share on Facebook
Tweet
Follow us
Share
Share
Share
Share
Share

Filed Under: News Tagged With: Right Column - Primary Sidebar

Reader Interactions

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • ጃዋርና በቀለ መታሠራቸው ተሰማ June 30, 2020 09:17 am
  • አገራዊ መድረክ ውጪ ድብቅ ውይይትን አንቀበልም June 17, 2020 06:57 am
  • ዴክሳሜታሶን! የኮሮና መድሀኒት June 17, 2020 06:49 am
  • የሰኔ 14ቱ ቀለበታዊ የፀሃይ ግርዶሽ በኢትዮጵያ! June 17, 2020 06:38 am
  • የግብፅ የአባይን ውሃ ብቻዬን ልጠቀም ግትር አቋም ድርድር እንቅፋት ሆኗል June 10, 2020 07:15 am
  • የቴድሮስ “ሥልጣን” – የመጨረሻው መጀመሪያ!? April 12, 2020 02:48 am
  • በብዛት የትግራይ ተወላጆች የሚጠቀሙበት የኤርትራ ስደተኛ ካምፕ ሊዘጋ ነው March 18, 2020 08:37 pm
  • እየተፈረካከሰ ያለው አንጋፋው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ March 18, 2020 08:09 pm
  • ኮሮና አዲስ ጉድ መዘዘ – ከቻይና በፊት በአሜሪካ ቁጥራቸው የማይታወቅ ሰዎችን ቀጥፏል March 16, 2020 11:41 pm
  • የኮንዶሚኒየም ቤቶች በደላሎችና በመመሪያ ሰጪዎች ኔትዎርክ እየተቸበቸበ ነው! ታከለ የት ናቸው? March 9, 2020 10:18 am
  • ኤርሚያስ ለገሠ ከባለአደራ ተባረረ March 9, 2020 08:09 am
  • ድፍድፍ ሲቀል ይንሳፈፋል፤ ምሁር ሲዘቅት ይመራል፥ March 7, 2020 11:24 pm
  • ኢትዮጵያዊ ምን ይመስላል? በምንስ ይመሰላል? March 7, 2020 10:29 pm
  • WHY I WROTE “MONEY, BLOOD AND CONSCIENCE” March 4, 2020 11:15 pm
  • አድዋ፤ የጥቁር ሕዝብ ድል! March 2, 2020 11:24 am
  • ፊታውራሪ ገበየሁ ገቦ (አባ ጎራው) March 2, 2020 11:12 am
  • የኦነግ ሁለት መልክና ሦስት ግብሮች – ቃርሚያው ኃይል ቅጥር ነፍሰገዳይ ሆኗል February 25, 2020 11:26 pm
  • በቡራዩ “የጃል ማሮ” ፎቶ ጨረታ አፈናከተ፤ “ቡራዩ ሆኖ ከሃዲን ማሞካሸት አይቻልም” ነዋሪዎች February 17, 2020 09:13 pm
  • “ዲቃላ” የፍረጃ ፖለቲካ በኦሮሚያ የኃይል አሰላለፉን እየቀየረ ነው February 13, 2020 11:58 pm
  • “ከዚህ በኋላ ማናቸውንም በወንጀል ድርጊት ውስጥ የሚሳተፉ አካላትን” አንታገስም – ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ February 13, 2020 05:07 pm
  • “እኛ ማንም ተሳዳቢ እንዲመጣብን አንፈልግም” የጅማ ነዋሪ February 13, 2020 09:28 am
  • “ወላጆቻችሁ ሰላማዊ ሰልፍ በሕዝቡ ያስደርጉልን” – አጋቾች February 11, 2020 07:53 pm
  • “ወንጀል የፈጸመም ያስፈጸመም ተይዞ ለህግ ይቀርባል፤ ምርመራም ተጀምሯል” February 11, 2020 06:59 pm
  • ጃዋር ወደ መጨረሻው “የትግል” ስልቱ – አማራን ማበጣበጥ! February 10, 2020 11:54 pm

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2026 · Goolgule