• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

ለህወሓት ሽማግሌ የላከ ሰው በኢትዮጵያ ላይ መዓት ያወርዳል!

October 25, 2019 07:37 am by Editor Leave a Comment

በተለያየ አጋጣሚ ከሚያጋጥሙኝ አስተያየቶች አንዱ ጃዋር መሃመድን መነጋገሪያችን ማድረጉን እንተው፤ግለሰቡ የሚሰጠንን አጀንዳ አንስተን በመተንተን ሰውየው የሚፈልገውን ክብር በመስጠት ተፅኖ ፈጣሪነት እንዲሰማው አናድርግ የሚል ነው። በግሌ ስራየ ብሎ ሰውን ማጉላትንም ሆነ ሆን ብሎ ሰውን ማሳነስን ብቻ አላማ አድርጎ መጓዙ የብልህ መንገድ አይመስለኝም። ጠቃሚው ነገር የሰው ስራ የሚያመጣው ተፅዕኖ ላይ ትኩረት አድርጎ መነጋገሩ ይመስለኛል። በዚህ ሁኔታ ግባችን ግለሰቦች ሳይሆኑ የግለሰቦች ሃሳብ እና አካሄድ የሚያመጣው በጎ ወይ መጥፎ ተፅዕኖ ነው። በጎ ወይም መጥፎ ተፀዕኖ ያመጣውን የሰዎችን ስራ በተመለከተ ስንነጋገር የሰዎችን ስም ማንሳታችን ደግሞ አይቀርም። በጎውን ስራ ስናወድስ፤ መጥፎው ስራ ወደ ባሰ መጥፎ እንዳያድግ ልንነጋገርበት ስናነሳሳው ከግለሰቦች ጋር የተለየ ፀብ ወይም ፍቅር ስላለን አይደለም።

ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነኝ ዝም ብሎ ለማለፍ ሞክሬ ያልቻልኩት የጃዋር ንግግር ነው። ንግግሩን ሰምቼ ዝም ብሎ ማለፉ ያቃተኝ ደግሞ ግለሰቡ በርካታ ስሜታዊነት የበዛው ተከታይ ያለው ሰው በመሆኑ ንግግሩ የሚያመጣው ተፅዕኖ በጎ ስላልመሰለኝ ነው። የዚህ ንግግር አንድ በጎ ጎን አቶ ጃዋር መስመሩ ከህወሃት ጋር መሆኑን በግልፅ ማሳወቁ ብቻ ነው። ለዛሬው ፅሁፌ መነሻ የሆነኝ የግለሰቡ ንግግር የተደረገው በኦሮምኛ ቋንቋ “OMN” በተባለው ሚዲያ ላይ ነው። ንግግሩ ከኦሮምኛ ወደ አማርኛ ሲተረጎም ይህን ይመስላል፤

“በደቡብም በምስራቅም ሄጃለሁ። ብዙ ሰዎች ፈርተው አይናገሩትም እንጅ አቋማቸው ከህወሃት የተለየ አይደለም። ፖለቲካ ያስተማሩኝም የብዙ ፓርቲዎች አመራር፣ ምሁራን፣ ወጣቶችም ጭምር በተለያየ ዘዴ አዋርቻቸዋለሁኝ። በይዘት ህወሃት የሚያራምደውን ፌደራላዊ ፖለቲካ ይደግፋሉ። እኛም አሁን ከህወሃት ጋር የሚያጣላን የታክቲክም ሆነ የስትራቴጅ ልዩነት የለም። ህወሃቶች ፌደራሊስቶች መሆናቸውን በተደጋጋሚ በተግባርም በአቋምም አሳይተዋል። ድሮ ብዙ ተባብለናል። ያለፈው አልፏል። እርግጠኛ ሆኜ የምናገረው ግን በአብይ ዙሪያ ካሉት ሰዎች መካከል አብይን ከልብ የሚደግፉ በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች ናቸው። በስም ሁሉ ልጠራቸው እችላለሁ። አሁን ኦሮሞ ማድረግ ያለበት ለስትራቴጅክ አጋሮቹ አጋርነቱን ማሳየት ነው። ሽማግሌም ቢሆን ልከን ዋናውን ስትራቴጅያዊ ወዳጅ አብሮን እንዲሰራ እንሞክር። አብይ ብቻውን ነው እየሄደ ያለው። እንደተናገርኩት በጣት የሚቆጠሩ ናቸው አጠገቡ ያሉት።” (መስመር የእኔ)

ይህን ንግግር በፍጥነት ወደ አማርኛ መልሰው ለህዝብ ይፋ ያደረጉት የተለያዩ የትግራይ ሚዲያዎች ናቸው። ተናጋሪው ወደ ምስራቅ እና ምዕራብ መጓዙን ሲናገር የተጓዘው ወደ ደቡብ/ምስራቅ ኦሮሚያ ይሁን ወደ ደቡብ/ምስራቅ ኢትዮጵያ ግልፅ አይደለም።ከተናጋሪው የቆየ በሚዲያ ለሚደረግ ንግግር ጥንቃቄ ያለማድረግ፣ ተረጋግቶ እና አስቦ ያለማውራት ባህሪ ተነስቶ ለገመገመ ደግሞ ደቡብ/ምስራቅ የሚለው አባባል ደቡብ/ምስራቅ የሚለውን አቅጣጫ ለመጠቆም ሳይሆን ወደ ብዙ ቦታ ተዘዋውሬ ሰዎች አነጋግሬያለሁ ለማለት ሲሆን ይችላል።

ተናጋሪው ኦሮሚያ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ፖለቲከኛ በመሆኑ እያወራ ያለው በኦሮሚያ ስላነጋገራቸው ሰዎች ነው ብለን ብንነሳ እየተባለ ያለው በኦሮሚያ ውስጥ ህወሃት ያራምደው የነበረው የፌደራሊዝም ፖለቲካ በእጅጉ ይወደዳል ነው። ይህ ማለት ኦሮሚያ ክልል በህወሃት ምርጫ ይሰየም የነበረ ርዕሰ መስተዳደር በመናፈቅ እየዋተተች ነው ማለት ነው። የኦሮሞ ፖለቲከኞች የኦሮሚያ ክልል ህወሃት በሚያሰማራቸው ህወሃታዊ ዘራፊዎች መዘረፉ ስለቀረበት አዝናነው ሊሞቱ ነው ማለት ነው።

ምስራቅ የተባለው በምስራቅ ኢትዮጵያ ነው ከተባለ ደግሞ የሶማሌ ክልል ምሁር፣ ፖለቲከኛ ወጣት ህወሃት ያደርገው የነበረውን ፌደራላዊ ፖለቲካ ይደግፋል ማለት ነው። በሌላ አባባል የሶማሌ ምሁር፣ ፖለቲከኛ እና ወጣት አብዲ ኢሌ እና ህወሃት እጅ ለእጅ ተያይዘው ያነበሩትን የፌደራሊዝም ፖለቲካ የሚደግፍ ነው ማለት ነው። ይህ ማለት የሶማሌ ፖለቲከኛ፣ ወጣት እና ምሁር የጄል ኦጋዴንን ሲኦል በመናፈቅ መዋተት ውስጥ ነው ማለት ነው። የሶማሌ ህዝብ በህወሃት ጀነራሎች የኮንትሮባንድ ንግድ ዘረፋ ናፍቆት እየተቸገረ ነው ማለት ነው። የሶማሌ ሴቶች በቀን በብርሃን በመሃል ከተማ መደፈርን የመሰለን “አክብሮት” ያመጣላቸውን ፌደራሊዝም እየናፈቁ ነው ማለት ነው።

ሕወሃት ያነበረው ፌደራላዊ ፖለቲካ ተናጋሪው እንደሚያስበው የደቡብ/ምስራቅ ጉዳይ ስላልሆነ ሰፋ አድርገን ስናየው በጋምቤላ በህወሃት ጀነራል እና ደራሽ ኢንቨስተር መሬትን መዘረፍ፣ የሲጋራ መግዣ የማያክል ገንዘብ ከፍሎ ለሚመጣ የውጭ ኢንቨስተር መሬትን አስረክቦ መፈናቀል፣ ህወሃት በሾመው አሻንጉሊት አስተዳዳሪ መተዳደር ባጠቃላይ የህወሃት የገንዘብ ሳጥን መሆን ነው። ለጋምቤላዎች ህወሃት ያነበረው የፌደራል ፖለቲካ ለኑዌር ወግኖ አኙዋክን መቸፍጨፈ፤ አለያም ኑዌር እና አኙዋክ ወንድማማችነቱን ረስቶ ለደመኝነት እንዲፈላለግ ማድረግ ነው።

የህወሃት የፌራሊዝም ፖለቲካ በአማራ ክልል ሁኔታ እንየው ከተባለ ለምለም መሬትን ለህወሃት አስረክቦ፣ የማልቀሻ እና መዝፈኛ ቋንቋን ሳይቀር ህወሃት የሚመርጥበት የባርነት አለም ውስጥ ቋንጃን ተቆርጦ መንፏቀቅ ነው። የህወሃት ፌደራላዊ ፖለቲካ ለአማራ ህዝብ በረከት ስምኦን በተባለ ኤርትራዊ ገዥ እግር ስር ተደፍቶ ውርደት መጋት አለያም አለምነው መኮንን በተባለ የአሽከር አሽከር አሻንጉሊት አስተዳዳሪ ያልተገራ አፍ መሰደብ ነው።

የህወሃት ፌደራሊዝም በአማራ ክልል መዲና ባህርዳር ከተማ ህወሃት በቀለሰው እስርቤት በህወሃት ገራፊ በፌሮ መገረፍ ነው። የህወሃት ፌደራላዊ ፖለቲካ በአማራ ክልል በተቀለሰ እስርቤት አማራ ሱሪውን አወልቆ ራቁቱን እንደቀረ፣ አከርካሪው የተሰበሰ ሽባ እንደሆነ እየተነገረው የበላው በአፉ እስኪመጣ በህወሃት መኳንንት ተዘቅዝቆ የሚሰቀልበት ማለትነው። የህወሃት ፌደራላዊ ፖለቲካ ለደቡብ ክልል ፖለቲከኛ በአንድ ህወሃት ቀላጤ ደብዳቤ መሾር፤ የህወሃት ባስልጣናትን ዘመድ አዝማድ በአንድ ሌሊት ከበርቴ የሚሆንበትን መንገድ ከፍቶ ዳርቆሞ ማየት ነው።

የህወሃት ፌደራሊዝም ዘጠኙም ክልል ጀግናው ህወሃት በትግርኛ ፅፎ ያሰናዳውን መመሪያ በየቋንቋው ተርጉሞ ህወሃት እንደወደደ ለማስፈፀም ሽር ጉድ ማለት፤ ለባርነት መታጠቅ ነው! የህወሃት ፌደራሊዝም ማለት የሶስት አባል እና የአምስት አጋር ፓርቲዎች ካድሬዎች የህወሃትን መንበር ተሸክመው “አሜን አሜን” ሲሉ ማለት ነው። የህወሃት ፌደራሊዝም ማለት መለስ ዜናዊ የእግዜር ታናሽ ተደርጎ ተቆጥሮ የተናገረው ቃል በዘጠኙም ክልል ካድሬዎች እንደወረደ ሲነገር ማለት ነው።

የህወሃት ፌደራሊዝም ማለት ህወሃት የጠላውን ዜጋ በሌሊት ይሁን በቀን፣ በእግር ይሁን በፈረስ ከፈለገው ክልል አምጥቶ ማዕከላዊ አስገብቶ ጥፍሩን ሲነቅል፣ በፌሮ ጀርባውን ሲተለትል፣ ዘር እንዳይተካ ሲያኮላሽ፣ግብረ ሰዶም ሲፈፅም፣ ሴት በርብርብ ስትደፈር ማለት ነው። ህወሃት ፌደራሊስትነቱን በተግባር አስመስክሯል ሲባል “ይህ አረመኔያዊ ተግባር ስሙ የፌደራሊዝም ፖለቲካ ይባላል” ብሎ መናገር ነው፤ ይህ ደግሞ ለእብደት መዋሰን ነው! ከህወሃት ጋር ስትራቴጃዊ አጋር ነኝ ማለት የዘረፋ፣ የአይን አውጣነት፣ የሰብዓ መብት ጥሰት አጋር ነኝ ማለት ነው።

በርግጥ የህወሓትን አረመኔነት ለመገንዘብ ከኢትዮጵያ ህዝብ አጠገብ ተቀምጦ ህወሃት ባሳረረው ማሳረረር ሳቢያ ከእስትንፋሱ የሚወጣውን የምሬት ጭስ ማየት ይጠይቃል። በህወሃት ዘመን ወደ ኢትዮጵያ ዝር ለማለት ቀርቶ ለማሰብ የማይደፍር ራሱን ጠባቂ “ታጋይ” ህወሃት በኢትዮጵያ ህዝብ አካል እና አእምሮ ውስጥ ስላስቀመጠው የማይሽር ጠባሳ ሊያውቅ አይችልም። እንዲህ ያለው “ታጋይ” ትናንት ህወሃትን ሲታገል የነበረው ከአትላንቲክ ማዶ ነፍሱን በጨርቅ ቋጥሮ በተቀመጠ፣ መራራ በደል ባልቀመሰ ማንነቱ ስለነበረ ያለፈውን እንደዋዛ ለመተው አይቸገርም።

በመሆኑም አቶ ጃዋር በምድረ-አሜሪካ ሆኖ ህወሃትን ታገልኩ ባለበት ዘመን ስለ ህወሃት ስላለው ነገር ሁሉ እንደ መፀፀት በሚቃጣው መልኩ እንደ አለፈ ውሃ እንዲተለው ይፈልጋል። እኛ የህወሃትን አረመኔያዊ ገፅታ ሁሉ እዚችው ቁጭ ብለን ያየን ኢትዮጵያዊያን ግን ህወሃትን መታገላችን ከበቂ በላይ በሆነ ምክንያት የተነሳ የተደረገ ነበርና የሚያፀፅተን፣ እንደ አለፈ ውሃ እንዲረሳልን የምንፈልገው ታሪክ አይደለም።

ይልቅስ ባሰብነው ቁጥር የምንኮራበት የታሪካችን ገፅ ነው! ወደፊትም ህወሃታዊነት የሚያንሰራራ በመሰለን ጊዜ ሁሉ ከቀድሞ በበረታ ጥንካሬ ለመታገል እጅ ለእጅ የምንያያዝ ባለምክንያት እምቢ ባዮች ነን እንጅ “የትናንቱን እርሱልን እና እንታረቅ” የምንል አጥነተ-ቢስ ልፋጭ ስጋዎች አይደለንም። ትላንት ያለ ምክንያት የጮኽ ብቻ “የትናነትቱን እርሱልኝ” ይላል፤ ትናንት በበቂ ምክንያት የታገለ ባለ አእምሮ በታገለው ባላጋራው ፊት አይሽረከረክም።

ከሁሉም በላይ የባላጋራችንን የህወሓትን ማንነት አሳምረን እናውቃለን። ህወሃት ስልጣኑን ካስቀማው ባላጋራው ጋር አይደለም አንድ አጭር የትችት አርቲክል ከፃፈበት ሰው ጋር የእውነት እርቅ አይታረቅም። በህወሃት እልፍኝ የእውነት እርቅ የለም! ህወሃት ከነገሩ ሁሉ አጥንት አለው! ጠላቱ እንታረቅ ባለው ሰዓት ሁሉ የሚታረቅ ደጅ ወጥቶ የተቀመጠ ልብ የለውም። የሆነ ሆኖ የህወሃት እግር ስር ተንከባሎ ማሩኝ ማለት፣ አመድ ነስንሶ ማቅ ለብሶ፣ድንጋይም ተሸክሞ ለእርቅ የህወሃትን ደጅ ማንኳኳት ይቻላል። መታወቅ ያለበት አበይት ጉዳይ ግን ህወሃት ጥፋቱን አምኖ ለመስተካከል ባልሞከረበት፣ ጭራሽ ሃገሪቱን ለባሰ ብጥብጥ ለመዳረግ ታጥቆ በሚሰራበት በዚህ ወቅት “ሽማግሌ ልኬም ቢሆን ከህወሃት ጋር እታረቃለሁ” ማለት ለኢትዮጵያ ህዝብ የጠብ ደብዳቤ መፃፍ ነው!

መስከረም አበራ

Print Friendly, PDF & Email

60

SHARES
Share on Facebook
Tweet
Follow us
Share
Share
Share
Share
Share

Filed Under: Opinions Tagged With: jawar, Right Column - Primary Sidebar, tplf

Reader Interactions

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • ጃዋርና በቀለ መታሠራቸው ተሰማ June 30, 2020 09:17 am
  • አገራዊ መድረክ ውጪ ድብቅ ውይይትን አንቀበልም June 17, 2020 06:57 am
  • ዴክሳሜታሶን! የኮሮና መድሀኒት June 17, 2020 06:49 am
  • የሰኔ 14ቱ ቀለበታዊ የፀሃይ ግርዶሽ በኢትዮጵያ! June 17, 2020 06:38 am
  • የግብፅ የአባይን ውሃ ብቻዬን ልጠቀም ግትር አቋም ድርድር እንቅፋት ሆኗል June 10, 2020 07:15 am
  • የቴድሮስ “ሥልጣን” – የመጨረሻው መጀመሪያ!? April 12, 2020 02:48 am
  • በብዛት የትግራይ ተወላጆች የሚጠቀሙበት የኤርትራ ስደተኛ ካምፕ ሊዘጋ ነው March 18, 2020 08:37 pm
  • እየተፈረካከሰ ያለው አንጋፋው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ March 18, 2020 08:09 pm
  • ኮሮና አዲስ ጉድ መዘዘ – ከቻይና በፊት በአሜሪካ ቁጥራቸው የማይታወቅ ሰዎችን ቀጥፏል March 16, 2020 11:41 pm
  • የኮንዶሚኒየም ቤቶች በደላሎችና በመመሪያ ሰጪዎች ኔትዎርክ እየተቸበቸበ ነው! ታከለ የት ናቸው? March 9, 2020 10:18 am
  • ኤርሚያስ ለገሠ ከባለአደራ ተባረረ March 9, 2020 08:09 am
  • ድፍድፍ ሲቀል ይንሳፈፋል፤ ምሁር ሲዘቅት ይመራል፥ March 7, 2020 11:24 pm
  • ኢትዮጵያዊ ምን ይመስላል? በምንስ ይመሰላል? March 7, 2020 10:29 pm
  • WHY I WROTE “MONEY, BLOOD AND CONSCIENCE” March 4, 2020 11:15 pm
  • አድዋ፤ የጥቁር ሕዝብ ድል! March 2, 2020 11:24 am
  • ፊታውራሪ ገበየሁ ገቦ (አባ ጎራው) March 2, 2020 11:12 am
  • የኦነግ ሁለት መልክና ሦስት ግብሮች – ቃርሚያው ኃይል ቅጥር ነፍሰገዳይ ሆኗል February 25, 2020 11:26 pm
  • በቡራዩ “የጃል ማሮ” ፎቶ ጨረታ አፈናከተ፤ “ቡራዩ ሆኖ ከሃዲን ማሞካሸት አይቻልም” ነዋሪዎች February 17, 2020 09:13 pm
  • “ዲቃላ” የፍረጃ ፖለቲካ በኦሮሚያ የኃይል አሰላለፉን እየቀየረ ነው February 13, 2020 11:58 pm
  • “ከዚህ በኋላ ማናቸውንም በወንጀል ድርጊት ውስጥ የሚሳተፉ አካላትን” አንታገስም – ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ February 13, 2020 05:07 pm
  • “እኛ ማንም ተሳዳቢ እንዲመጣብን አንፈልግም” የጅማ ነዋሪ February 13, 2020 09:28 am
  • “ወላጆቻችሁ ሰላማዊ ሰልፍ በሕዝቡ ያስደርጉልን” – አጋቾች February 11, 2020 07:53 pm
  • “ወንጀል የፈጸመም ያስፈጸመም ተይዞ ለህግ ይቀርባል፤ ምርመራም ተጀምሯል” February 11, 2020 06:59 pm
  • ጃዋር ወደ መጨረሻው “የትግል” ስልቱ – አማራን ማበጣበጥ! February 10, 2020 11:54 pm

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2026 · Goolgule